ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሞክሩትን አስጠነቀቁ – ሙሉ ቪዲዮውን ይመልከቱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ለማደናቀፍ በሚሞክሩና በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ክምችት ላይ በተሰማሩት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም ረቂቅ በጀትን በሙሉ ድምፅ ባፀደቀበት ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው ይህን የተናገሩት።

በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረገው ውይይት በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሙሉ ቪዲዮውን ይመልከቱ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኑበታል።
ደህንነትን በተመለከተ

“አሁን የተፈጠረውን ለውጥ የማይደግፉ አካላት አሉ። በተለያዩ ቦታዎች ይህን ለውጥ ለማደፍረስ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። መንግሥት እነኚህን ጠንቅቆ ያውቃል ይቀጫቸዋልም” ብለዋል።

”እነዚህ አንቅስቃሴዎች ባዶ መሻቶች ናቸው። በእንዲህ አይነት ተግባራት ውስጥ የሚሳተፉ ፖለቲከኞች ነገር ሲሞት እና ሲድን አያውቁም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የግብር ሥርዓትን ማዘመን

መንግሥት መሰብሰብ የሚገባውን ያህል ግብር መሰብሰብ እንዳልቻለ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በቀጣዩ ዓመት መንግሥት የግብር መሰብሰቢያ ሥርዓቱን በማዘመን እና ባለሃብቶች የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ የግብር ገቢን እንጨምራለን ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያዘዋውሩ እና የሚያከማቹ ሰዎች ገንዘባቸውን ወደ ባንክ እንዲያመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅረበዋል። የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል በተለያየ መንገድ ያፈሩትን ገንዘብ ወደ ባንክ ለሚያመጡ ግለሰቦች ህግን የተከትለ ምህረት ይደረግላቸዋል። ይህንን በማይፈጽሙት ላይ ግን ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በተመለከት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከአገር ውስጥ ባንኮች ብቻ እስከ 400 ቢሊዮን ብር ገደማ መበደራቸውንና በርካታ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሚያወጡት ዋጋ በላይ እዳ እንደተከማቸባቸው ገልጸዋል። በዚህም አዲስ የልማት ድርጅቶች መገንባት ከመጀመር ይልቅ የተጀመሩትን መጨረስ ይመረጣል። መጨረስ ያልተቻሉትን ደግሞ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል ብለዋል።
የቤቶች ግንባታ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በአዲስ አበባ የቤት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የቤቶች ግንባታው በሚፈለገው ፍጥነት እና ጥራት እየተካሄደ አለመሆኑን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አጽንዖት ሰጥተው እንደተናገሩት መንግሥት የዜጎችን የቤት ፍላጎት ማሟላት አይችልም ብለዋል። ስለዚህም የግሉ ዘርፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፤ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሳካት መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተባብሮ ይሰራልም ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን በተመለከት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ተለይቶ መታየት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሆነ ዜጎች በአማካይ 60 በመቶ ገቢያቸውን ለምግብ ያውላሉ፤ በዚህም የምግብ ዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጣር መንግሥት ይሰራል ብለዋል። መንግሥት የዜጎች የገቢ ምንጭ እንዲጨምር በመስወራት እና ብዙ በማምረት የምግብ ዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የውጪ ምንዛሪ

በመጀመሪያ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት አገሪቱ 10 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት እቅድ የያዘች ቢሆንም እስካሁን ማሳካት የተቻለው ግን ሲሶው ያህል ብቻ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ አሁን የተከሰተውን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እነደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም ከወዳጅ አገራት ጥሬ ዶላር በባንኮቻችን ውስጥ በማስገባት የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ሙከራ ተደርጓል። በዚህም በጥቁር ገብያ የዶላር ዋጋ ቀንሷል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
የትምህርት ጥራት

በኢትዮጵያ በተለያዩ ደረጃዎች በትምህርት ላይ ያሉ 29 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዳሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ አገሪቱ ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣ ተናግረዋል። ”የምናስተምረው ተማሪ ጥራት ያለው ትምህርት ካላገኘ እየከሰርን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትምህርት ጥራት የማይነካው ዘርፍ የለም ስለዚህም የትምህርት ጥራት ችግርን ሊቀርፍ የሚችል ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክረ-ሃሳብ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በማብራሪያቸው መጨረሻ ላይ በውጪ አገራት የሚኖሩ ዜጎችን ያካተተ ለአገር እድገት ይበጃል ያሉትን ምክረ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት በምክረ-ሃሳብ በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ወደ ሦስት ሚሊዮን ይገመታል ያሉ ሲሆን፤ በትንሹ አንድ ሚሊዮን ያህሉን ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚከተለውን ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

1.ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንዳሉት በቦርድ የሚመራ እና ወጪ እና ገቢው በትክክል የሚታወቅ ትረስት ፈንድ በማቋቋም ዲያስፖራው በየቀኑ አንድ ዶላር እንዲለግስ እንጠይቃለን ብለዋል። በዚህም አገሪቱ ቢያንስ በየቀኑ 1 ሚሊየን ዶላር ልታገኝ እንድምትችል ተናግረዋል።

2.ከዚህ በተጨማሪም በውጪ አገራት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ በባንኮች ብቻ እንዲልኩ ጠይቀዋል። ይህም በአገሪቱ የሚታየውን ውጪ ምንዛሪ ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።

3.የግል ባለሃብቶች ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን እንዲፈጥሩ እና የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፍል የዜግነት ግዴታቸውን ይወጡ ጥሪያ አስተላልፈዋል።

Source: BBC Amharic News

AddisNews is not responsible for the contents or reliability of any other websites to which we get contents from and provide a link and do not necessarily endorse the views expressed by them.

Article first published here

Recommended For You

About the Author: EthioForum